Genesis 22

አብርሃም ተፈተነ

1ከዚህ ሁሉ በኋላ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) አብርሃምን ፈተነው፤ “አብርሃም!” አለው። እርሱም “አቤቱ አለሁ” አለ።

2እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ “የምትወድደውን አንዱን ልጅህን፣ ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያ ምድር ሂድ፤ እኔ በማመለክትህ በአንዱ ተራራ ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው” አለው።

3በማግስቱም ጧት አብርሃም ማልዶ ተነሣ፤ አህያውን ጭኖ፣ ሁለት አገልጋዮቹንና ልጁን ይስሐቅን ይዞ፣ ለመሥዋዕት የሚበቃውን ዕንጨት ከቈረጠ በኋላ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወዳመለከተው ቦታ ለመሄድ ጕዞውን ጀመረ፤ 4በሦስተኛው ቀን አብርሃም ቀና ብሎ ቦታውን ከሩቅ ተመለከተ፤ 5አገልጋዮቹንም “እናንተ አህያውን ይዛችሁ እዚህ ቈዩን፤ እኔና ልጄ ግን ወደዚያ ሄደን ለእግዚአብሔር ሰግደን እንመለሳለን” አላቸው።

6አብርሃም ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን ዕንጨት ወስዶ፣ ልጁን ይስሐቅን አሸከመው፤ እሳቱንና ቢላዋውንም ራሱ ያዘ። ሁለቱም አብረው ሄዱ። 7ይስሐቅም አባቱን አብርሃምን፣ “አባቴ ሆይ” አለው።

አብርሃምም፣ “እነሆኝ፤ አለሁ ልጄ” አለው።

ይስሐቅም፣ “እሳቱና ዕንጨቱ ይኸው፤ ነገር ግን የሚቃጠለው መሥዋዕት የት አለ?” ብሎ ጠየቀ።

8አብርሃምም፣ “ልጄ ሆይ፤ ለሚቃጠለው መሥዋዕት የሚሆነውን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል (ኤሎሂም ይሬህሎ)” አለው። ሁለቱም አብረው ጕዟቸውን ቀጠሉ።

9እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወደ አመለከተው ቦታ እንደ ደረሱ፣ አብርሃም መሠዊያ ሠራ፤ በላዩም ላይ ዕንጨት ረበረበ፤ ልጁን ይስሐቅንም አስሮ በመሠዊያው ዕንጨት ላይ አጋደመው። 10ከዚያም ልጁን ለማረድ እጁን ዘርግቶ ቢላዋውን አነሣ። 11የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ ግን ከሰማይ፣ “አብርሃም፤ አብርሃም፤” ብሎ ጠራው፤

አብርሃምም፣ “እነሆ፤ አለሁ” አለ።

12እርሱም፣ “እጅህን በብላቴናው ላይ አታሳርፍ፤ ምንም ጕዳት አታድርስበት፤ እነሆ፤ እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) እንደምትፈራ ተረድቻለሁ፤ ልጅህን፣ ያውም አንዱን ልጅህን ለእኔ ለመስጠት አልሳሳህምና” አለው።

13አብርሃም ቀና ብሎ ተመለከተ፤ በቍጥቋጦ መካከልም ቀንዶቹ የተጠላለፉ አንድ አውራ በግ ከበስተ ኋላው አየ፤ ወደዚያው ሄዶ በጉን አመጣና የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ሠዋው። 14ከዚህም የተነሣ አብርሃም የዚያን ስፍራ ስም፣ “እግዚአብሔር ያዘጋጃል (ያህዌ ይርኤ)” ብሎ ጠራው፤ እስከ ዛሬም ድረስ፣ “በእግዚአብሔር (ያህዌ) ተራራ ላይ ይዘጋጃል” ይባላል።

15 የእግዚአብሔርም (ያህዌ) መልአክ አብርሃምን ከሰማይ ዳግመኛ ጠራው፤ 16እንዲህም አለው፤ “እግዚአብሔርም (ያህዌ) በራሴ ማልሁ አለ፤ አንዱን ልጅህን ለእኔ ለመስጠት አልሳሳህምና፣ 17በርግጥ እባርክሃለሁ፤ ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት፣ እንደ ባሕር ዳር አሸዋም አበዛዋለሁ። ዘሮችህም የጠላቶቻቸውን ደጆች ይወርሳሉ፤ 18ቃሌን ስለ ሰማህ የምድር ሕዝቦች ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ።”

19ከዚያም አብርሃም ወደ አገልጋዮቹ ተመለሰ፤ ተያይዘውም ወደ ቤርሳቤህ ሄዱ፤ አብርሃምም በቤርሳቤህ ኖረ።

የናኮር ልጆች

20ከዚህ በኋላ እንዲህ ተብሎ ለአብርሃም ተነገረው፤ “ሚልካም ደግሞ የልጆች እናት ሆናለች፤ ለወንድምህም ለናኮር ወንዶች ልጆችን ወልዳለች። 21እነርሱም የበኵር ልጁ ዑፅና ወንድሙ ቡዝ፣ የአራም አባት ቀሙኤል፣ 22ኮዛት፣ ሐዞ፣ ፊልዳሥ፣ የድላፍና ባቱኤል ናቸው።” 23ባቱኤልም ርብቃን ወለደ። ሚልካ ለአብርሃም ወንድም ለናኮር የወለደችለት እነዚህ ስምንት ወንዶች ልጆች ናቸው። 24ከእነዚህም ሌላ የናኮር ቁባት ሬናሕ ደግሞ ጥባሕ፣ ገአም፣ ተሐሽና ሞክሳ የተባሉ ወንዶች ልጆች ወለደችለት።

Copyright information for AmhNASV